05/07/2026
ከቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ....
"በሬ ሆይ ሳሩን እንጅ ገደሉን መች አየህ!"ይባል የለ?
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ አርቲስቶችና አዝማሪዎች አካባቢ ለጊዜያዊ ጥቅምና ለዕይታ (views) ማሳደጊያ ሲባል፣ ዓለምን በታሪኩና በጥበቡ ያስደመመውን የታላቁን ፃድቅና ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላን ስም ካልዋለበት በማዋል የታሪክ መዛባትን ለመፍጠር ሲታትሩ እየታዘብን እንገኛለን።
ማንነታቸውና አመጣጣቸው በውል እየታወቀ፣ በየማኅበረሰቡ ቤት በጧት እየዞሩ በዘፈን መልክ ልመናን እንደ ሥራ ቆጥረው ለሚንቀሳቀሱ አባ ውዴ ወይም ሃሚና ለተባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቅዱስ ላሊበላን ስም መስጠት እጅግ አሳፋሪ፣ የድንቁርና ጥግና የታሪክ ፍልሰትን የሚያስከትል ተግባር ነው።
ይህንን መሰል ስም ማጥፋት በሕግም ጭምር የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል መሆኑ ታውቆ፣ እነዚህ አካላት በአስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እያሳሰብን ላጠፉት ጥፋት በሕዝብ ፊት ቀርበዉ ወይም በማንኛዉም ሚዲያ ቀርበዉ ይቅርታ እንዲጠይቁ ከወዲሁ እናሳስባለን!
ከሁሉም በላይ ሊሰመርበት የሚገባው እውነታ፦
እነዚህ አካላት በቅዱስ በቅዱስ ላሊበላ ከተማም ሆነ በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በምንም መልኩ የማይታወቁ፣ በታሪክም ሆነ በጂኦግራፊያዊ መገኛቸው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት የሌላቸው መሆኑን ነው። በመሆኑም፣ በልመና ባህል ውስጥ የሚታዩትን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በገናናው ንጉሥ ስም መሰየም የዓላማ እና የይዘት መደበላለቅን የሚፈጥር ስህተት ነው።
፪. የቅዱስ ላሊበላ ሕዝብ እውነተኛ ማንነት እና የማኅበረሰቡ እሴት
የቅዱስ ላሊበላ ሕዝብ ታሪክን፣ ሃይማኖትንና የሥራ ባህልን አጣምሮ የያዘ ኩሩ ማኅበረሰብ ነው። የአካባቢው ነዋሪ መገለጫዎች የሚከተሉት መሆናቸውን ማንም ሊመሰክረው የሚችል ሐቅ ነው፦
ታታሪነትና ሥራ ወዳድነት፦ የቅዱስ ላሊበላ ሕዝብ ልመናን ፍጹም የሚጸየፍ፣ በራሱ ላብና ጥረት መኖርን እንደ ትልቅ ክብር የሚቆጥር በሥራ ብቻ የሚያምን ማኅበረሰብ ነው።
እንግዳ ተቀባይነትና ርኅራኄ፦ቅዱስ ላሊበላን መሠረት በማድረግ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ አቅመ-ደካሞችና ችግረኞች በአካባቢው ቢገኙም፣ ሕዝቡ እነዚህን ወገኖች በደግነት፣ በፍቅርና በሕክምና በመንከባከብ የሚይዝ እንጂ የሚያገል አይደለም።
ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ፣ አንዳንድ ነገሮችን በጥልቀትና በሰፊው ማየት የተሳናቸው፣ ለታሪክ ግድ የሌላቸውና ችኩል አካላት፣ ታሪካዊውን የቅዱስ ላሊበላን ማኅበረሰብ ከልመና ተግባር ጋር አያይዘው ለማይመጥነው ስም በመስጠት የታሪክ ብልሹነት ለመፍጠር ሲታትሩ እየታዘብን እንገኛለን ።
ማሳሰቢያ
የአገር ቅርስና የታሪክ አሻራ የሆነውን የጻድቁን ንጉሥ ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ስም ማጥፋትና ማጠልሸት፣ የማኅበረሰብን ክብር የሚነካ ከመሆኑም በላይ በሕግ አግባብ በስም ማጥፋት (Defamation) ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ሊታወቅ ይገባል።
የታሪክ ስህተትንና ፍልሰትን እያመረቱ ያሉት አካላት ካልተቆጠቡ፣ ጉዳዩ ወደ ሕግ አደባባይ የሚወሰድ መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን።በመሆኑም፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ይህንን ታሪካዊ ስህተት በመፈጸም የገናናውን የቅዱስ ላሊበላን ስም ካልዋለበት በማዋልና የታሪክ ፍልሰትን በመፍጠር በማኅበረሰቡ ላይ ማዕበል ያስነሱ፣ ስም ያጠለሹና ያዋረዱ አካላት በሙሉ የፈጸሙትን ስህተት በአደባባይ አምነው በመቀበል፣ ጉዳዩ በሚመለከተው ማኅበረሰብ ፊትና ስሙን ባጠለሹበት በማንኛውም የሚዲያ አማራጭ (ማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ መደበኛ መገናኛ ብዙኃን) ላይ በአስቸኳይ ይፋዊ የይቅርታ ጥያቄ እንዲያቀርቡ በጥብቅ እንጠይቃለን፤ ይህ ካልሆነ ግን የታሪክ መበላሸትን ለመከላከልና የማኅበረሰቡን ክብር ለማስጠበቅ ሲባል ጉዳዩን በሕግ አግባብ እስከ መጨረሻው የምንገፋበት መሆኑን እናሳስባለን።
ታሪክ የጋራ እሴት ነው፤ እሱን መጠበቅ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ የሞራል ግዴታ ነው፡፡
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን።
©️የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር ጽ/ቤት