10/04/2022
ለሰሞኑ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ሊያውም በተከበረው በረመዳን ወር የተጀመረው ሰላትን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው የማራቅ ዘመቻ ከጀርባው ማን እና ምን ይኖር ይሆን የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ ሰንብቷል።
በእርግጥ እንደሀገር ያለንበት ብዙም ያልተረጋጋ አውድ ከሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ጀርባ ሁሉ "ምክንያቱ ምን ይሆን" በሚል ተርታውን ህዝብ ሳይቀር ስነልቦናን የሚፈታተኑ ስሌቶች እንዲሰራ ማስገደድ ከጀመረ ቆይቷል። ከየትኛውም ወጣ ያለ ድርጊት ጀርባ "ምን ታስቦ ይሆን? " የሚለው የሁሉም የለትከለት ጥያቄ እየሆነ ነው። ይህ በህዝብና በመንግስት መካከል በጎ የሚባል ግንኙነት አይደለም።
የተበታተነ የሚመስለውን ሙስሊም ተማሪዎችን ከስግደታቸው፣ ከፆማቸው እና ከትምህርታቸው የማሰናከል ዘመቻ አስተዳደራዊ መልክ ይዞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ መግለጫ እንደሰጠበት ማምሻውን አነበብን። ይህ የሃይማኖት ነፃነትን የሚጋፋ፣ የሀገራችንን ህግና የሴኩላሪዝም መርህ አንሻፎ የተረጎመ፣ ወቅትና ሁኔታን ከግምት ያላስገባ የተሳሳተ አመራር እየተሰጠ እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በማሳተፍ ዛላቂ መፍትሄ የሚሰጥበት አካሄድ እንዲጀመር አጥብቄ እጠይቃለሁ። የተማሪዎችን የሃይማኖት ነፃነት የሚገፉ ጫናዎችም እንዲቆሙ እጠይቃለሁ። ሁሉም አካላት በስክነትና በምክንያት እንዲመሩም ጥሪዬን አቀርባለሁ።