25/12/2025
- ኢዜማ
በኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን ዐራት መቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሰርቫንቶች) እንዳሉ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም 1900 የመንግሥት ተቋማት መኖራቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ መካከል 84 በመቶ የሚኾኑት በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ተቋማት የሚሠሩ ናቸው፡፡
ይኽም በታችኛው የመንግሥት መዋቅሮች የሚገኙ ሠራተኞች በርካታ ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ያመለክታል፡፡ በታችኛው መዋቅር ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች የብዛታቸውን ያህል ማኅበረሰቡን በሚገባ ማገልገል እንዳልቻሉ ሀገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው የዐደባባይ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሞኑን ደግሞ ከብልጽግና ፓርቲ በተዋረድ በተላለፈ ትዕዛዝ በፌደራል፣ በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ለሕዝብ አገልግሎት መሥጠት በሚገባቸው የሥራ ሰዓት የፓርቲ ስብሰባ እያከናወነ ይገኛል፡፡ የፓርቲው አመራሮችም ይህንኑ ተግባራቸውን እንደ ጀብድ እና ስኬት በመንግሥት ሚዲያዎች ሲተርኩ እየታዘብን ነው።
ይህ ሁኔታ በዘመነ ኢሕአዴግ በስፋት ይስተዋል የነበረ ሲኾን፤ ብልጽግና ፓርቲም ትምህርት ያልወሰደበት የስህተት መንገድ ኾኖ ቀጥሏል፡፡ ፓርቲያችን ኢዜማ ባለፈው ሳምንት ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በወርሀ ግንቦት ለሚከናወነው ሀገርአቀፍ ምርጫ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን ለፓርቲ ሥራ መጠቀሙን በአስቸኳይ እንዲያቆም ያሳሰበው፤ መሰል የስህተት መንገዶች እንደ ሀገር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን በማቀጨጭ አምባገነንነትን እንደሚያነግሡ ስለሚገነዘብ ነው፡፡
ከሰሞኑ ባገረሸው በመንግሥት የሥራ ሰዓት እና ሃብት የፓርቲ ስብሰባ የማድረግ አባዜ መሠረታዊ የሕግ የበላይነት ድንጋጌዎች ተጥሰዋል፤ ዜጎችም ዕለታዊ አገልግሎት ተነፍገው የመልካም አሥተዳደር በደል ደርሶባቸዋል፤ በቀላል ስሌት በወረዳ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ያባከኑትን የሥራ ሰዓት ከዚህ በታች እንደሰፈረው መመልከት ይቻላል፡፡
በአንድ ወረዳ ውስጥ በአማካይ እስከ 300 የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ ፓርቲያችን ባደረገው የመረጃ ማጣራት ተገንዝቧል፤ በዚህም መሠረት ፓርቲያችን አዲስ አበባ በሚገኙ አስር ወረዳዎች ባደረገው ምልከታ ሠራተኞቹ በሥራ ሰዓታቸው ሊያሳልፉት ከሚገባው ከግማሽ በላይ የሆነውን የሥራ ሰዓት ለፓርቲ ስብሰባ ማዋላቸውን የተመለከትን ሲሆን በዚህም መሠረት በእነዚህ ወረዳዎች በአማካይ 150 የሚሆኑት ሠራተኞች ከ 37,500 በላይ ሰዓታትን በዐምስት ቀናት ብቻ እንዳባከኑ ለመረዳት ችለናል። ይህ አይነት ስብሰባ በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚደረጉ በገዢው ፓርቲ የተለያዩ የማኀበራዊ ትሥሥር ገጾችና ሚዲያዎች እየተገለጹ መሆኑን ወስደን ስሌቱን ከ 5000 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ያሉባቸውን ተቋማት ከመረመርን ደግሞ የሚባክነው ሰዓት መጠን ብዙ መሆኑ እና አገልግሎት ማግኘት የሚገባው ማኅበረሰብ ምሬት ምን ያህል እንደሆነ መገመት አዳጋች አይደለም።
የመንግሥትን የሥራ ሰዓት ለፓርቲ ሥራ ማዋል ሳያንስ የተበደሉት የሥራ ሰዓታት እና የተጉላላው አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ እንግልት አንፃር ስንመዝነው ጥፋቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ ዜጎች በአመለካከት የሚመስላቸውን የፖለቲካ ድርጅት የመደገፍ መብታቸው ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ የለንም ሆኖም በሕዝብ ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥት ተቋማት የአንድ ድርጅት ተቀጥላ እንዲኾኑ ጫና ማድረግ ግን በሕግም ሆነ በሞራል ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ትምህርት ያልወሰደው ከኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፤ ከዐምስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ የምርጫ ወቅት መቃረብን ተከትሎ መንግሥታዊ መዋቅርን እና ሀብትን ባልተገባ መንገድ ለእራሱ ጥቅም በማዋል ሕገወጥ ስብሰባ ያደርግ የነበረ ሲሆን ከዚህ ተግባሩ ከመቆጠብ ይልቅ እንደውርስ ሃጢያት ይዞ መንጎዱን ያሳያል፡፡ ይህም ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነትና ለዘላቂ የሕዝብ ጥቅም ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላለው ሕዝብ በአካባቢ ምርጫ ወኪሎችን ከመረጠ ከ 20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ መሠረታዊ የፌደራሊዝም መገለጫ የኾነው የዜጎች በታችኛው መዋቅር የመወከል መብት ባልተጠበቀበት በዚህ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን ተጨማሪ በደል ቆም ብሎ እንኳን ለማሰብ አለመቻሉ የበለጠ ድርጊቱን አሳፋሪ ያደርገዋል።
ስለኾነም አሁንም በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ እንዳሳወቅነው ሁሉ ፓርቲው ከዚህ እና መሰል ተግባሮቹ እንዲቆጠብ ጥሪ እናደርጋለን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንን ጉድይ በአንክሮ በመከታተል ከዚህ ድርጊቱ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎች ከአገልግሎት ጋር የተገናኘ በደልን ከፍ ባለ ደረጃ በመከታተል ተጠያቂ እንዲያደርግም እንዲሁ እንጠይቃለን። ኢዜማ መሰል የፓርቲ እና መንግሥት መጣበቅ የሚያመጣውን ችግር በተረዳ መልኩ የፓርቲውን መዋቅር የሚያጠናክር የድርጅት ክንፍ እና የፖለቲካ ሁነቶችን የሚከታተል የመንግሥት ክንፍ አወቃቀርን የመረጠበት ዋነኛው ምክንያት ይህንን ሰቅዞ የያዘንን ችግር ለማስወገድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
ታሕሳስ 14/2018 ዓ.ም.